በሐረር ከተማ ሸዋበር አካባቢ በተለምዶ ታይዋን በሚባል የገበያ ስፍራ በደረሰው የእሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም ታስቦ የተዘጋጀ የሐብት ማፈላለጊያ ማስፈጸሚያ እቅድ ላይ በአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መልሶ በማቋቋም በዘላቂነት ወደ ስራ ለመመለስ የተዋቀረው ግብረ ሃይል ም/ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ያህያ በአደጋው የንብረት ጉዳት የደረሰባቸው አካላት ተወካዮችና ከባለድርሻዎች ጋር በሐብት ማፈላለጊያ (Fund Raising) ማስፈጸሚያ እቅድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ይህ ሀብት የማሰባሰብ ስራ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ስራው በአጭር ጊዜ የተቀናጀና ውጤታማ ስራ በመስራት ለተጎዱ ወገኖቻችን ቶሎ መድረስ እንዲቻል ለሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት በእቅዱ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የራሳቸውን ሃላፊነት ተወጥተው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ቶሎ እንዲቋቋሙ በትኩረት መስራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይም በስፋት መክረዋል።
በተጨማሪም የንብረት ጉዳት ደረሰባቸው አካላት ተወካዮች የአደጋው ያደረሰውን የጉዳት መጠንና ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት የመለየት ስራ በአፋጣኝ በማጠናቀቅ ወደ ሃብት ማሰባሰቡ ስራ መግባት እንደሚያስፈልግም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በእቅዱ ላይ ድርሻ ያላቸው አካላት አደጋ የደረሰባቸውን ዜጎቻችን መልሶ ለማቋቋም የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም በውይይቱ ተመላክቷል።
በመጨረሻም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ም/ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ያህያ ለሁሉም የግብረ ኃይሉ አባላት የስራ አቅጣጫ በመስጠት ውይይቱ ተጠናቋል።