በሐረሪ ክልል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ቀደም ሲል አውጥቶት በሥራ ላይ የነበረውን የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 43/2003 በማሻሻል ላይ መሆኑን ተገለፀ።
ቢሮው እንደገለጸው መመሪያውን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ለግዥ የሚመድቡት በጀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ግዥ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ግዥ ለመፈጸም የሚኖራቸውን የግዥ ዘዴ አማራጮችን ለማስፋት፣ የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች በመንግሥት ግዥዎች ላይ በመሳተፍ የሚኖራቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ፣ በግንባታ ግዥዎች አፈጻጸም ሂደት ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፍቱ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ፣ ግዥ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ግዥ ላይ ከሚያውሉት የገንዘብ መጠን ተመጣጣኝ የጥራት ደረጃ ያለውን ግዥ መፈጸም የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ቀደም ሲል ለአፈጻጸም ግልጽ ያልነበሩ የአፈጻጸም ሥርዓቶችን ግልጽ በማድረግ የመሥሪያ ቤቶችን የግዥ ሂደት ለማሳለጥ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ማሻሻያ የተደረገባቸው አንቀጾች በርከት ያሉ ሲሆኑ ከእነዚሀ መካከል ለግንባታ ዘርፍ፣ ለዕቃ ግዥ፣ ለምክር አገልግሎት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚፈጸም ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ግዥ ለመፈጸም ተደንግጎ የነበረው የገንዘብ ጣሪያን እንደየዘርፉ ከነበረበት መጠን ወደ እጥፍ የማሳደግ ረቂቅ ሃሣብ ቀርቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በውስን ጨረታ እና በአካባቢ ማስታወቂያ ለሚፈጸም ግዥ ከዚህ በፊት የነበረው ጣሪያ ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን ጥቃቅን ግዥዎች በቀጥታ ሲገዙ የተቀመጠው ጣሪያም ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠውለታል፡፡
የጨረታ አከፋፈትና የሂደቱ ሥርዓትም ማስተካከያ የሚደረግበት ሲሆን የጨረታ አሸናፊዎች ውል ስለሚገቡበት ሁኔታም የተሻሻለው ረቂቅ መመሪያ ይደነግጋል፡፡ መመሪያው በተጨማሪም የመንግሥት ግዥ ባለድርሻ አካላት ስለሚኖራቸው ሚናም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ረቂቅ መመሪያው ሥራ ላይ ሲውል ቀደም ሲል የነበሩ የአሠራር ክፍተቶችን በመድፈን ግዥዎችን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመፈጸም የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ሥራን ለማከናወን ማነቆ የሚሆኑ ችግሮችንም ያስወግዳል የሚል እምነት አለ፡፡
በመመሪያው ማሻሻያ መድረክ የክልሉ ሴክተር መ/ቤት ኃላፊዎች እና ተወካዮች እንዲሁም የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡ መመሪያው በየደረጃው ግብአት ከተሰበሰበ በኋላ ዳብሮና ተስተካክሎ በሥራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል፡፡