የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ ክልሉ በሚያመነጨው ኢኮኖሚ ልክ ገቢ መሰብሰብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተባለ።
በገቢ አሰባሰብ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተደራጀ ሁኔታ ለመቅረፍ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮን ጨምሮ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን፣የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮና የፕላንና ልማት ኮሚሽን ቢሮ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው በየጊዜው የአፈፃፀም ሂደት ሲገመግሙ እንደነበር ይታወሳል።
በዛሬው ዕለትም በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊ በአቶ መሐመድ ያህያ ሰብሳቢነት የክልሉ የ6 ወራት የገቢ አሰባሰብ እና የዕቅድ አፈፃፀም በተመለከተ ኮሚቴው በጋራ ገምግሟል።
በግምገማውም የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ፣የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤትና የከተማ ልማትና ኮንስራክሽን ቢሮን የግማሽ አመት አፈፃፀም ተመልክተዋል።
የገቢ አቅምን በማሳደግና የክልሉን የልማት ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረግ ጥረት በ2016 በጀት አመት በልዩ ሁኔታ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በሚካሄድ ስራ ባለፉት ስድሰት ወራት ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች ብር 969 ሚሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 1‚095 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መቻሉ ተገልጿል፡፡
ከቀረበው ሪፖርትም በመነሳት ከታሪፍ ማሻሻያዎች፣ ቫትና ዊዝሆልዲንግ፣ የአካባቢ ልማት ፕላንና የደረሰኝ ቁጥጥርን በተመለከተ በቀጣይ መሻሻል መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ገቢን የሚሰበሰቡ ተቋማት የገቢ አቅማቸውን በአግባቡ ለይተው እቅዳቸውን በመከለስ የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በየጊዜው የዘርፉን አፈፃፀም መገምገም እንዳለባቸው አቅጣጫ የኮሚቴው ሰብሳቢው አቶ መሐመድ ያህያ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ።
በተጨማሪም የክልሉን የልማት ፍላጎት ለማሟላት እንዲያስችል የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ለማሳደግ በቀሪ ወራት የተሻለ ገቢ ለመሰብስብ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግም በመግለፅ ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት የተቀናጀና የተናበበ የአሰራር ስርአት በመዘርጋት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት መሰብሰቡ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ጋር በተያያዘ የአሰራር ስርአት ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማሻሻል እንቅፋት የሆኑ የህግ ማእቀፎችንና መዋቅሮችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ገደብ በማሻሻል እንዲያቀርቡና ወጪዎችና በመቀነስ ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመጨረሻም የመንገድ ትራንስፖርትና ልማት ቢሮ በዘርፉ ገቢን ከማመንጨት አንፃር ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች ያቀረቡ ሲሆን ሰብሳቢውም በቀጣይ በጥናት ላይ የተሞረከዘ የድጋፍ ፍላጎት እንዲያቀርቡ አቅጣጫ በማመላከት የዕለቱ መድረክ ተጠናቋል።