የ26ኛው ዓለም አቀፍ የሀረር ቀን በተመለከተ የተቋቋመው የካፒታል ፕሮጀክቶች ክትትል ኮሚቴ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው አካሄደ ።
የዓለም አቀፍ የሀረሪዎች የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ከአሁን በፊት በተለያዩ አለም አቀፍ በተለያዪ አህጉራት ሲከበር የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በታሪካዊቷ ሀረር ለ26ተኛ ጊዜ በደማቅ የሚከበር ይሆናል።
በአሉ ሀረር ላይ መከበሩ የመጪውን ትውልድ ብሩህ ተስፋና ራዕይ የሚያሳኩ ዘላቂ ፕሮጀክቶችና የልማት ሥራዎች መሰረት ለመጣል የሚያስችል ነው ፡፡ ምክንያቱም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ሀረሪዎች ፤ የሀረር ተወላጆችና ወዳጆች እንዲሁም አጎራባች ክልሎች ፤ እህትማማች ከተሞችና ህዝቦች የሚሰባሰቡበት በመሆኑ ፍቅርና መቻቻልን የሚያጠናክር ብሎም መልካም ገጽታ ፤ የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያጎለብት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው።
በመሆኑም የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የሀረር ቀን በሚፈልገውና በሚጠበቀው ደረጃ ለማሳካት የሚከናወኑ ተግባራት የተቀናጀና የተደራጀ አኳሃን ለመፈፀም እንዲያስችል ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች አንዱ የሆነው የካፒታል ፕሮጀክቶች ክትትል ኮሚቴ በየሳምንቱ መደበኛ ስብሰባው እያካሄደ ይገኛል።
በዚህም መሰረት በዛሬው ስብሰባ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ያህያና የፕሮጀክቱ ባለቤት ተቋማት አመራሮች በተገኙበት በባለፈው ስብሰባ ተቋማቱ እቅደቸውን ከልሰው እንዲያመጡ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተከለሰው እቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም በቤቶች ልማት፣በባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ፣በውሃና ፍሳሽ ቢሮና በግብርና በኩል ተለይተው የቀረቡ ካፒታል ፕሮጅክቶች ያሉበትን የአፈጻጸም ሂደት ላይ ተወያይተዋል።ከዚህ ጋር በተያያዘ የነባርና አዲስ ፕሮጀክቶች የዕቃ ገዥ ሂደት ላይ መክረዋል።
የፕሮጀክቶች ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ያህያ በቀጣይ ቀናት የእቅድ ድርጊት መርሃ ግብራቸው በደብዳቤ እንዲያሳውቁ፣ቅድሚያ የሚሰጣቸው ግዠዎች ተለይተው እንዲቀርቡ ገልፀው በሚቀርበው ድርጊት መርሃ ግብር መሰረት ፕሮጀክቶች የሚገመገምበት የመስክ ምልከታ ፕሮግራም እንደሚደርሳቸው አመላክተዋል።
በተጨማሪም የኢኮ ፓርክና ሌሎች ፕሮጅክቶችንም በሚመለከት ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በቅድሚያ ተለይተው ለግዠ ጽ/ቤት በጊዜ መቅረብ አንዳለባቸው አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባ ተጠናቋል።