ሐረር (መስከረም 28 ቀን 2019 ) ገኢትቢ— የሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግሥት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የመሠረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን፣ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ለማሻሻል ያለመ የማህበራዊ ተጠያቂነት የግንዛቤ ማስጨበጫና የምክክር መድረክ አካሄደ።
መድረኩ በሕዝቡና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ቀጥተኛ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ የመንግሥት አገልግሎቶች የዜጎችን እውነተኛ ፍላጎት መሠረት ያደረጉና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የጅንኤላ፣ አቦከር፣ አሚር-ኑር እና ሶፊ ወረዳዎች አመራሮች፣ አፈ-ጉባዔዎች፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሕያ አብዱረሒም እንደገለጹት የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በፌዴራል መንግሥትና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ትብብር የሚተገበር ወሳኝ አሠራር ነው። አሠራሩ በተለይም በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና እና በገጠር መንገድ ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ደረጃ በየጊዜው ለመገምገምና ክፍተቶችን ለመሙላት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም ይህ ሥርዓት ኅብረተሰቡ በአካባቢው በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ጥያቄዎችን በግልጽ እንዲያነሳ የአገልግሎት ጉድለቶችን እንዲያመላክትና በመፍትሔ አፈላላጊነት በባለቤትነት እንዲሳተፍ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በመድረኩ የማህበራዊ ተጠያቂነት፣ የበጀትና የፋይናንስ ግልጽነት እንዲሁም የቅሬታ አፈታት ሥርዓትን የተመለከቱ ገለጻዎች ቀርበዋል። በተጨማሪም የጅንኤላ ወረዳ የተሞክሮ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የወረዳ አስተዳዳሪዎችም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበው የማሻሻያ ግብረ-መልስ ተሰጥቷቸዋል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአራቱ ወረዳዎች የሚስተዋሉ የአገልግሎት አቅርቦት ማነቆዎችን በጋራ በመለየት አፋጣኝ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አመላክተዋል። በመጨረሻም የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዜጎች ችግሮችን ያለምንም ማመንታት በግልጽ በማንሳትና የመፍትሔ ሐሳቦችን በማጋራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።












